ራስን ፈትሾ ተገቢውን የእርምት እርምጃዎች መውሰድ ሰአቱ አሁን ነው::
ነዓምን ዘለቀ
ጠ/ሚንስትር ዶ/ር ዓብይ አህመድ ፣ ከከፍተኛ የብልጽግና ባለስልጣናት፣ እንዲሁም የካቢኔ ሚንስትሮች በጋራ መክረውና ዘክረው፤ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል የፓሊሲ አቅጣጫን በመከተል ሚዛናዊ እርምጃዎች ካልወሰዱ፤ በአገራችን ላይ ሊደርስ የሚችለዉን ከፍተኛ የቀውስ አዙሪት ለማስቆም የሚያዳግት ይመስለኛል። በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ ለተከሰተው ከሁለት የመከፈል ቅውስ መንስኤ በጥልቀትና በሰከነ አስተዋይ አእምሮ የተገመገመና በጥሞና የታሰበበት የመንግስት አቋም ስንጠብቅ፤ ጠ/ሚኒስትር ዓብይ ለካቢኔ አባላቶቻቸው በህዝብ ፊት ያደረጉትና ያለምንም ጥያቄም ሆነ አስተያየት እሳቸው ጀምረው እሳቸው የጨረሱት ብዙ ስህተቶች የተስተዋሉበት ገለጻ የተከሰተውን ችግር ለመፍታት የሚያስችል መፍትሄና አቅጣጫ የሚያመላክት አልነበረም። ይልቁንም ቀውሱንና ውጥረቱን የሚያባብስና ያሚያስቀጥል በመሆኑ ጠንካራ ደጋፊዎቻቸውን ሳይቀር በጣም ቅር አሰኝቷል፡፡ለዚህም አስተያየታቸው በቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠው በመረጃና በጥናት የታገዘ ተገቢ ምላሽም እንዲሁም ባለፉት ጥቂት ቀናት እየሆነ ያለው በጣም አስጊ ሁኔታ ማረጋገጫዎች ናቸው ፡፡
የሀገራችን ችግሮች መገለጫ እንዱ የጠንካራ ተቋማት እጥረት ነው። በዚህ ረገድ ጥንታዊቷ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክርስትያን በጣም የዳበረ፣ ሰፊና፣ ጥልቅ የአሰራር፣ የአካሄድ ስርአቶችና ወገች እንዳሏት፣ ይህን በአግባቡ እንደምትከተል፣ ተቋማዊ አሰራር እንዳላት፣ በሀገሪቱ ህግም መሰረት ህጋዊ ሰውነት እንዳላት የሚታወቅ ነው። እሁን ላይ በደረሰባት ትልቅ አደጋ ሳቢያ እንኳን በመላው አለም የሚገኙ አባቶች ጥሪ በማድረግ፣ በመሰብሰብ፣ አደጋውን ለመከላከል የተደረገው ሰፊ የጋራ ምክክር፣ እየታየ የሚገኘው የተረጋጋ አያያዝ፣ መብቶቹዋን ለማስከበር የወሰደችው ጠንካራ አቋምም ሆነ፣ የበሰለ፣ የሰከነ አካሄድ የተቋሟን ጥንካሬ የሚያሳዩ ገጽታዎች ናቸው። ተቋማት እንዲገነቡና እንዲጠናከሩ በተደጋጋሚ የሚናገሩት ጠ/ሚ አብይ ይህን እውነታ በአግባቡ ያጤኑት አይመስልም።በጠ/ሚ ዓብይ ለካቤኔ አባላት ባደረጉት ንግግርም ሆነ በቅድስት ቤተክርስቲያኗ ሲኖዶስ በተሰጠው መልስ፤ እንዲሁም በተለያዩ ጉዳዩን በቅርበት በሚከታተሉ የህብረተሰብ ክፍሎች፤ ሚድያና አዋቂዎች የተሰጡትን ትችቶችና አስተያየቶች ይዘት ዝርዝር ማቅረብና መገምገም የዚህ ጽሁፍ ዓላማ አይደለም። ዋናዉ የዚህ ጽሁፍ ዓላማ፤ ጠ/ሚ ዶ/ር ዓብይ ይህን የመሰለ የሀይማኖትና የቤተክርስቲያኑዋን አንድነት ብቻ ሳይሆን፤ የሀገርን ሰላምና ህልዉና፤ የሕዝብንም ደህንነት ሊያናጋ የሚችለውን ከፍተኛ የህብረተሰብ ቀውስ የተረዱበትና፤ መፍትሄ ለመስጠት አቅጣጫ የያዙበት ዘዴ የተሳሳተና ውጥረቱን አርግቦ በህጋዊ መንገድ እንዲፈታ የማድረግ ሃላፊነት ያለበት መሪ መውስድ የሚገባ አቋም እይደለም። ይህንም ለማለት እንድደፍር ያስገደዱኝን ዋና ዋና ምክንያቶችም ከእዚህ በታች ለማብራራት እሞክራለሁ፡፡
1ኛ። ለውጡ ከመጣ ጀምሮ ለጠ/ሚ አብይ ከፍተኛ ድጋፍና ተቀባይነት ያስገኘላቸው በወሰዱት በርካታ የለውጥ እርምጃዎችና እስደማሚ፣ ስኬታማ ግዙፍ ፕሮጄክቶች ሳቢያ ነው። ይህም በርካታ ተግዳሮችና ፈተናዎች ውስጥ ተዘፍቃ በምትገኝ ሀገር ውስጥ መሆኑ ክብርና አድናቆት የሚያስጣቸው ነው። ሆኖም ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፓርላማ በቀረቡባቸው እንዳንድ እለታት በህዝብ ውስጥ ለሚብላሉ ከፍተኛ የደህንነት ስጋቶች ጋር ተያይዘው ለሚቀርቡ ጥያቄዎች፣ በየጊዜው ከማንነት ጋር በተያያዘ የተከሰቱ ተደጋጋሚ የንጹሃን ዜጎች እልቂትና፣ መፈናቀል፣ ምክንያቶችን አስመልክቶ እልፎ አልፎ የሚሰጡአቸው አስተያየቶችና መልሶች የሚያንጸባርቁትም አቋም ፣ የሚሰነዙሯቸው የማይገቡ ኃይለቃላትና ግሳጼዎች፣ ተቃዋሚዎቻቸዉን ብቻ ሳይሆን ደጋፊዎቻቸዉንና ሕዝብንም ጭምር ሲያሸማቅቁ ፣ ሲያስደነግጡ አስተውለናል፡፡ በግልጽ የሚታዩ ጥሬ ሃቆችን የመሸፋፈንና የማድበስበስ፣ አመክንዮን በማፋለስ የማይገናኙ ጉዳዮችን የማገናኘት አዝማሚያዎች የሚታዩባቸው አካሄዶች፤ በውጭም ሆነ በሀገር በውስጥ ጠንካራ ድጋፍ ሲሰጣቸው የቆየውንና መሃል ላይ በግራና ቀኝ የተሰለፈዉን እምነት የጣለባቸውን ሀገር ወዳድና ሰፊ የሆነ ወገን ተስፋ እየቆረጠ፤ የድጋፋቸው መሠረት እንዲሸረሸርና እንዲቦረቦር እያደረገው መሆኑ በግልጽ ይታያል። ይህን እውነታ በቆራጥነትና በሀቅ ተጋፍጦ ማሻሻል ወደፊት ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚመጡ ችግሮችን በአግባቡ ከማስወገድ አልፎ ሌላ አማራጭ የሌለው እንደሆነ አምናለሁ።
2ኛ። ጠ/ሚ ዓብይ የፌደራል መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ መግባት፤ ህገ መንግስታዊ አግባብ እንደሌለው የተናገሩት ትክክለ ነበር። ነገር ግን የኦሮቶዶክስ ቤት ክርስትያን ውስጥ የተነሳውን ቀውስ አስመልክቶ ጠ/ሚ ዓብይ ለካቢኔያቸው በሰጡት ማብራሪያና መመሪያ ሁሉ ከዚህ በፊት ሲያደርጉት ከነበረው በተለየ መልኩ የተሰነዘሩት ሃይለ ቃል ለብዙዎች እስገራሚ፣ እስደንጋጭም ነበር። በህዝብ ፊት ለእሳቸው ገንቢ ሀሳብ ፣ አስተያየት፣ እንደ አስፈላጊነቱም ገንቢ ሂስ መስጠት ፣ ለሚጠበቅበት የካቤኔ አባላት ማስጠንቀቂያ መስጠት ለምን አስፈለገ? ካስፈለገም ከልካዩን ህግ አብራርቶ ያንን የሚጥስ ድርጊት መፈጸሙን ህግ ካለም ጠቅሶ አመላካች መንገድ ማቅረብ ሲቻል በዚያ መልኩ ለካቤኒ አበላት በግላጭ የወረደ መመሪያ ለብዙ ታዛቢዎች እኔንም ጨምሮ ገራሚ ያደርገዋል።
በሌላ በኩል የህግ የበላይነት ማስከበር ሃላፊነት የተጣለባቸው ጠቅላይ አቃቤ ህግ፣ ፌደራል ፓሊስ በክልል የጸጥታ ሃይሎች የሚደርሰውን የህግ ጥሰት ሲከላከሉ፡ የመእመናና የቀሳውትን የመብቶች ሲያስከብሩ አይደመጥም፣ አይታይም። የጠ/ሚ ጣልቃ እትግቡ ውሳኔ አነዚህን አካላት አይመለከትም ወይ? የሚል ጥያቄ ያስነሳል። መንግስትን የሚያስተዳድረው የፌደራል ህግ መንግስት በመላው ኢትዮጵያ ሉአላዊ ነው ይላል (supreme law of the land)። የፌደራል ህገ መንግስት የሚሰጠው መብት በክልል ባለስልጣኖች/ጸጥታ ሃይሎች ሲጣስ፣ ህጉን የሚያስከብረው የሚገባው የፌደራል መንግስት መሆኑ የታወቀ ነው። በቤተ ክህነት ጉዳይ ጣልቃ አለመግባትና የቤተ ክህነት መሪዎች መብትና ደህንነትን ማስከበር የተያያዙ ጉዳዮች ናቸው። የአንድ ክልላዊ መንግስት የጸጥታ ህይሎች የፌደራሉን ህግ በሚጥስ መልኩ የመንግስትና የሃይማኖት ልዩነት በጣሰ ሁኔታ ከአንድ ወገን ወግነው በሌላው ወገን ላይ ኢ-ህገ መንግስታዊ ገደብ፣ አፈና፣ እስር፣ ምርመራ በሚያካሂዱበት ጊዜ ይህን ህገ ወጥ ተግባር የማስቆም ሃላፊነት ያለባቸው የፌደራል አካላት (እዛው ስብሰባ ላይ የፍትህ ሚንስትር፣ የሰላም ሚንስትር ተገኝተዋል) እጃቸው ሰብስበው እንዲቀመጡ ማዘዝ ትክክለኛ ውሳኔ ሊሆን አይችልም። እንዲያውም አደገኛ መሆኑን እያየን ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ በአገሪቱ የፌደራል ህገ መንግስት የማይገዛ በመንግስት ውስጥ ሌላ መንግስት እንዲኖር እየተደረገ ይመስላል። ይህ እሰራር ደግሞ ለህወሃትም እንዳልበጀ የሚታወቅ፡ መዘዙም ጥልቅና ግዙፍ ይሆናል። ይህን እውነታ ብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ስጋት ወስጥ እየከተተና በእጅጉ እያሳዘነም መሆኑን የብልጽግና መሪዎችና የካቤኔት አባላት በጥሞና ሊያዩት ይገባል።
3ኛ። በእኔ እይታ ጠ/ሚኒስትር ዓብይ የኢትዮጵያን ታሪክ የሚገልጹባቸው አስተያየቶች እንዳንድ ጊዜ በተሳሳቱ ታሪካዊ መረጃዎችና የአንድ ጎንዮሽ ምልከታና ትርጓሜ ላይ የተመረኮዙ ይመስለኛል። እንድ የሀገር መሪ በተለይ የሚያስተዳድረዉን ሀገር ታሪክ ሲገልጽ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግና፤ ካስፈለገም የታሪክ አዋቂዎችን ምክር መስማቱ ተገቢ ነው። ለምሳሌ በካቢኔ ገለጻቸው ጊዜ፤ የዶ/ር ብረሃኑና አቶ ቀጄላ መርዳሳን የትግል ተሞክሮና ሂደት በሚመለከት የተናገሩት ትርክት አግባብነት የሌለዉም፤ እውነታውንም የማይገልጽ ስህተት ነው። የአሁኑ የኢዜማ መሪ (የቀድሞ የአርበኞች ግንቦት 7 ሊ/መንበር) ፕ/ሮ ብርሃኑም ሆነ የኦነግ አመራር አባል አቶ ቀጄላ መርዳሳ ጨምሮ፡ በርካታ የኢሕአፓ አባላት፣ ሌሎች ታጋይ ድርጅቶች መሪዎችና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በተለይም ወጣቶች የተሳተፉበትና በርካቶችም ለሀገራቸው ፍቅር ሲሉ የህይወት መስዋእት የከፈሉበት የዘመናት ተከታታይ የነጻነትና የዲሞክራሲ ትግልን አስተዋጽዖ እንዲህ አቅልሎ ማየት በምንም መሥፈርት እግባብ አይመስለኝም።
4ኛ ሌላው የጠ/ሚ ለካቤኔ አባላት የተሰጠ ማብራሪያና መመሪያ የሚገኝ ስህተት የመንግስት ለውጦችን በሚመልከት የተሳሳተ ግንዛቤ ያለበት ነው፡።በልዩ ልዩ ሀገሮች በመፍንቅለ መንግስት የመጣ መንግስት በሌላ መፈንቅለ መንግስት ሲተካ አይተናል። በህዝብ አመጽ የመጣ መንግስትም በሌላ ሕዝብ አመጽ መተካቱን የቅርብ ጊዜ እንኳን በርካታ አብነቶች አሉ። የአጼ ህይለ ስላሴ ስርአት የነ ጀ/ል መግስቱን ያከሸፈው የ1953ቱ መፈንቅለ መንግስት ለምን ሆነ ብለው ቢጠይቁና በግዜው የለውጥ እርምጃዎች ቢያደርጉ ኖሮ ሌላ ወደ ህዝባዊ አብዮት ባላመራ ነበር። ይሁን እንጅ ንጉሡን ከስልጣናቸው ያወረዳቸው በዋነኛነት ወታደሩም የተሳተፈበት በየካቲት 66 የተቀጣጠለው ታላቅ የሕዝብ ማእበል እንጂ ጠ/ሚንስትሩ እንዳሉት የወታደሩ መፈንቅለ መንግሥት ለብቻው አልነበረም። ይህ ህዝባዊ ማእበል የተቀሰቀሰውና በሀገሪቱ በሞላ ተቀጣጥሎ የንጉሡን ሥርአት የገረሰሰው በሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ተሳትፎ ቢሆንም፤ በዋነኛነት የተመራው በወጣቱ፤ በምሁራኑና በሰራተኛዉ ከፍተኛ ትግሎች ነበር፡፡ “በወደቀ ግንድ ምሳር ይበዛበታል” እንዲሉ ወታደሩ በ 11 ኛው ሰዓት ለመውደቅ ሲንገዳገድ የነበረውን የንጉሡን ሥርአት ገፍቶ ሊጥል የቻለው ብረት ስለያዘና በወቅቱ በደንብ የተደራጀ ሀይል እሱ ብቻ ስለነበረ ነው። በእዚህ የኢትዮጵያ ታሪክ ላይ በርካታ የተጻፉ መጻሕፍትም አንዳቸዉም ንጉሡ የወደቁት በመፈንቅለ መንግሥት ነው አይሉም።
የደርግ ኢሠፓ መንግስትም ሊወድቅ የቻለው በወታደራዊ ጡንቻው ፣ በስራዊቱ ብዛትና በአዛዦቹ ጥራትና ጀግነነት ማነስ ሳቢያ አልነበረም። በአመዛኙ አገዛዙ ከህዝብ ጋር ሆድና ጀርባ ስለነበረ፣ በዋነኝነትም ህዝባዊ ቅቡልነቱንና ድጋፉን በማጣቱ፤ ይህም ሁኔታ ለወያኔ ሰራዊት ግስጋሴ መንገዱ ስላመቻቸለት፤ በሩን ስለከፈተለት እንጂ “ወያኔ በጦርነት ብልጫ ኖሮት ሊያሸንፍ” በመቻሉ አይደለም፣ አልነበረምም። ስለሆነም እዚህ ላይ ዋናው ነጥብ የአንድ መንግስት ትልቁ ጥንካሬ የሚመነጨው ከህዝባዊነቱ ፣ ከቅቡልነቱ፡ ርእታዊና ፍትሃዊ ከመሆን ፣ ከህግ የበላይነትና፣ አግባብ ያላቸውን የህዝብ ጥያቄዎች ህዝብን ኣክብሮ መመለስ ከመቻሉ እንጂ፤ የታንክና የመድፍ ፣ ሌሎችም ዘመናዊ መሳሪያዎች ከመታጠቅ፣ ከስራዊት ብዛት ጋር የተያያዘ እንዳልሆኑ የብዙ ስርአቶች የውድቀት ታሪክ ያሳያሉ፡፡እንዲሁም በምርጫ ወደ ስልጣን መምጣት በራሱ ብቻውን የመንግስትን ጥንካሬና ቀጣይነት እንደማያረጋግጡ ከበቂ በላይ የታሪክ ተሞክሮዎችና ማሳያዎች አሉ።የሩቁን ትተን የቅርቡን የዛሬ 4 ኣመት ተኩል እሳቸው የሚገኙበት የለውጥ ቡድን ወደ ስልጣን ሊያመጣ የቻለውን እንኳን ብንወስድ ከኢሳት እስከ ኦኤምን፣ ከኤርትራ በርሃ ከተነሳ የነጻነት ታጋዮች ትግልና መስዋእትነት፣ በአማራ፣ በኦሮሞና በሊሎች አካባቢዎች ክልል የተደረጉ ሰፊ የህዝብ እምቢተኝነት ትግሎች፣ ስርአቱን ያሽመደመደ ከኢኮኖሚያዊ ጦርነት (ለምሳሌ ጠ/ሚኒስትር አብይ ወደ ስልጣን እንደመጡ እንዲቆም ጥያቄ ያቀረቡበት የውጭ ምንዛሬ እቀባ እለም አቀፍ ዘመቻ፣ ራሳቸው)፣ በልዩ ልዩ መደበኛና ማህበራዊ ሚዲያዎች ሲደረጉ የነበሩ የስነ ልቦናና ሁሉን አቀፍ ትግሎና ዘመቻዎች ዉጤት መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም፡፡ ። እኤአ 2018 የመጣው ለውጥ በሚልዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያን በቆራጥነት ለ 27 አመታት የታገሉለትና ብዙ ሺዎች ብዙ አይነት ከባድ መስዋእትነት የከፈሉበት ዉጤት ነው። የእንድ ብሄር ልሂቃን የበላይነት በሁለንተናዊ መልኩ እስፍኖ የነበረ ዘረኛና ዘራፊ ስርኣትን ቅቡልነት ያሳጣው፣ የመጨቆኛ ምስሶዎችን ገዝግዞ ያናገው ፣ ዶ/ር አብይና ጓደኖቻቸው በኢህአዴግ ውስጥ ትግል እንዲያደርጉ ያደፋፈረና ያነሳሳው የበርካታ ህይሎች ትግሎች ድምር (cumulative) ውጤት ነው። ተመስሳዩን ለማሳየት በአንድ የጦርነት አውድማ መደበኛ ጦር፣ ልዩ ጦር፣ አየር ወለድ፣ ታንከኛ፣ መድፈኛው ፣ አየር ሃይል ፣ በአሁን ጊዜ ደግሞ ድሮኖች የየራሳቸው ድርሻ እንደሚያበረክቱት ሁሉ የተራራውን ጫፍ ሄዶ የያዘው የእግረኛ ስራዊት የድሉ ብቸኛ ተዋናይ እንደማያደርገው ሁሉ እነዚህ ዘርፈ ብዙ ትግሎችና መስዋዕትነቶች የህወት መሩን አንባጋነን አገዛዝን ለመጣል ያደረጉት አስተዋጽዖ ሊቃለል አይገባውም፡፡
ለማጠቃለል የሀራችንን ህመሞች ለማከም ከልብ ከተፈለገ በየጊዜው የሚገጥሙንን ቀውሶች በጥሞና ገምግሞ፣ ከሁሉም ገጽታዎች፣ አቅጣጫዎች በመመልከት፣ በሕዝቡ መሀል ግልጽ ውይይቶችን ማካሄድ፣ በአንገብጋቢ ጥያቄዎች ላይ የጋለ ክርክር በመቻቻልና በመከባበር ያለሰቀቀን እንዲካሄድ ማደፋፈር አስፈላጊ ነው፡፡በመሠረቱ አንድ መሪ ሁሉን አዋቂ መሆን አይጠበቅበትም። በሁሉ ጉዳዮች ከራሱ እይታና ሃሳብ ላይ ተነስቶ አቋም መያዝ፣ ውሳኔ መስጠት ለ21ኛው ክፍለ ዘመን ተቀጣጣይ፣ ውስብስብ፣ በፈጣኑ ተለዋዋጭ፣ ኢ-ተገማች (ቪዩሲኤ/VUCA) ክስተቶች በበዙበት ሀገራዊና አለም አቀፍ አውድ፣ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ለአመታት ለዘለቁ ችግሮች የብቻዉን መፍትሄ ማምጣት አይቻለዉም፤ አይጠበቅበትምም። በተለይም በቀውስ ውስጥ ስትታመስ ለቆየች ሀገር፣ ከጦርነት ወጥቶ ፣ የሕዝብ ቁስል ገና ባልተጠገነበት ሁኔታ፣ ከዚህ ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶችና ችግሮች ለማገገም ብዙ ትግል እንደሚጠይቅ ግልጽ ነው፡፡ ስለሆነ፣ ጠ/ሚ ዓብይ አዕምሮአቸዉን ክፍት አድርገው ይህንን ሁኔታ በውል ተገንዝበው፤ የአማካሪዎችና የካቤኔ አባላት ግልጽ ውይይትና ክርክር በማመቻቸ፤ በስሎ ተመክሮ በወጣ የውሳኔ አሰጣጥ የችግሮች/ቀውሶች አፈታት መንገድ ቢከተሉ፣ የሕዝብንም የልብ ትርታና ጥያቄዎችን በትክክል እያዳመጡ፤ ነገሮችን በሰከነ ሁኔታ አመዛዝኖ መፍትሄ የመፈለግ አካሄድ ቢከተሉ ለእርሳቸዉም ለሀገርም ጠቃሚ ይሆናል፤ ስህተት ከመሥራትም ይድናሉ፡፡
ይህን ጽሁፍ በይፋ እንድጽፍ ያነሳሳኝ፣ሀገራችን ከኣንድ ቀውስ ወደ ሌላ ቀውስ፤ ከአንድ ፈተና ወደ ሌላ ፈተና እየተሸጋገረች የምትሰቃይበት ምክንያቶች አንዱ በተፈጥሮዋ ወይም በሕዝቦቿ አለመታደል ሳይሆን፤ በዋነኛነት የሚመራዉን ሕዝብ አስተባብሮ በመምራት ችግሮቿን ከስር ነቅሎ የሚጥልላት ፈውስ የሚሆኑ አስተውሎ ያላቸው መሪዎች እስከዛሬ ባለማግኘቷ ነው ብየ ስለማምን ነው። ይህ ለዉጥ ሲጀምር በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያን በዶ/ር ዓብይ ላይ እምነት በመጣል አሁን ሊያልፍላት ነው፤ መሪ እያገኘች ነው ብለው ነበር፤ለኢትዮጵያ ጥሩ ራይ ሰንቀው ለውጡን በስተመጨረሻም ቢሆን የተቀላቀሉትና የተራራውን ጫፍ የወጡት ዶ/ር አብይ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ከፍተኛ ክብርን፣ ድጋፍ (እኔም በርካታ የትግል ጓዶቼን ጨምሮ) ሲያደርጉ ቆይተዋል። አሁን ግን ያ ተስፋ እኔን ጨምሮ በብዙ ወገኖች ዘንድ እየተመናመነ የመጣ ይመስላል፡ይህ ለውጥ ህወሀት የተከለዉን ዘረኛ ስርአት ከስሩ ነቅሎ መጣል ባለማቻሉ ዜጎች በሀገራቸው ባይተዋር የሚደረጉበት እኩልነት፣ ፍትህና የህግ የበላይነት የተነፈጉበት ያለፈው ግፈኛ ስርአት በበርካታ የሀገሪቱ አካባቢዎች እንደቀጠለ ነው። ይባስ ብሎ ጠባብ ብሄረተኝቱ፤ ንጹሀን በማንነታቸው እየተለዩ መጨፍጨፉ፤ መፈናቀሉ የባሰበት፣ ኢትዮጵያውያን ዜጎች በገዛ ሀገራቸው እንደ ሁለተኛ ዜጋ ተሸማቀው እንዲኖሩ ብቻ ሳይሆን ፣ በማንነታቸውም በየጊዜው እንግልት፣ በደል፣ አድሎ የተስፋፋባቸው ሁኔታዎች በበርካታ የሀገሪቱ አካባቢዎች ስር እየሰደዱ ነው፡፡ እንዲሁም በአዲስ አበባም ሆነ በልዩ ልዩ ክልሎች ከላይ እሰከ ታች የተንሰራፋው ሙስናና ሌብነት፣ የአስተዳደር በደሎች፣ ኢ-ፍትሃዊነትን፣ አድሎአዊነት ሳይገታ በመቀጠሉ የህዝብ ምሬት እየተባባስ ለመሆኑ ከበቂ በላይ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ዛሬ ላይ የሚታየው ስር የሰደደ ከጠባብ ብሄረተኝነት የሚመነጭ ዘረኝነት ከአራት አመት በላይ የዘለቀው ለውጥ ሊፈውሰው ያልቻለ የነቀዘ ስርአተ መንግስትና የ 27 አመት “የብሄር ፖለቲካ” በመያያዙ ጭምር ነው። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ላይ የሚደርሰው ጥቃትም የሚያመለከተው ይህንኑ ነው፤ ለውጥ ያመጣል የተባለው ስርአት ትልቅ ፈተና ውስጥ አየገባ መሆኑን ነው።
ብዙ ሚልዮኖች የታገሉበት፣ ብዙ ሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያን ጀግኖች በህይወታቸው ሳይቀር መስዋእትነት የከፈሉበት፤ ብዙ ፈተናዎችን የተጋፈጡበት፡ ብዙ አይነት ዋጋ ብዙዎች የከፈሉበት ለውጥ አስተውሎ ያለው አመራር በማጣት አቅጣጫዉን እንዲስትና አሁንም እንዲመክን የሚፈልግ ሀገሩ ወዳድ ኢትዮጵያዊ ሊኖር አይችልም፣። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ሀይማኖት ላይ ያንዣበበዉ አደጋ ቶሎ መፍትሄ ተገኝቶለት ካልቆመም መዘዙ ሀገርና ህዝብ ሊሸከሙት አይችሉም። ግዜው ሳይመሽ ውስጥን/ራስን መፈተሽ፣ መመርመና የእርምት እርምጃዎች መውሰድ የሚገባ ወሳኝ ምእራፍ ላይ ደርሰናል። ዘርፈ ብዙ ማህብራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፓለቲካዊና ከደህነት ጋር የተያያዙ ስጋቶች በስፋት በሚገኙበት፣ ከማንነት ጋር ተያይዞ በደረሱ ጥቃቶች ሳቢያ የተፈጠሩ የህዝብ ብሶቶችና ተቃውሞች፣ ቀውሶችም እየተደራረቡ፣ እየጠነከሩ፣ እየተመጋገቡም በሚገኙበት በዛሬዋ ኢትዮጵያ ምንም አይነት ሃይል ሊያስቆመው የማይችል እጅግ አደገኛ የታሪክ መጋጠሚያ ጫፍ ነጥብ (Tipping point) ላይ ከመድረሳቸው በፊት ክቡር ጠ/ሚንስትር ዶ/ር ዓብይና ሌሎች የመንግስትና የብልጽግና መሪዎች የገጠመውን ቀውስ ግዝፈት በጥሞና ማጤን ይገባቸዋል። በአጣዳፊነት ስሜትና በአስተውሎ ሀገራዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ እንደ እንድ ሃላፊነት እንዳለበት ኢትዮጵያዊ ዜጋ በትህትና እጠይቃለሁ። የመጣውን አደጋ ለማስቆም በስኬት ይወጣሉ ብዬ ተስፋ በማድረግ ነው፡፡ የእሳቸው ስኬት የሀገራችን የኢትዮጵያ የህዝባችን ስኬት ነዉና። (ክፍል ሁለት ይቀጥላል)
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ! ለሀገራችን ሰላም ያዉርድልን!
ነዓምን ዘለቀ ፣ ጥር 27 ቀን 2015
ቨርጂኒያ ዩስ አሜሪካ
ብዙ ነገር ተነገር አገሪቷ ወዴት እየሄደች እንደሆነ ያስታውቃል ጥላቻና ወደ ዘር እየሄደች ነው ። ከባለፈው ስርአት በምን ተለየ የስም ለውጥ ነው ያየነው ለምሳሌ ወያኔ ልዩ ጥበቃውን አጋዚ ሲለው ነበር አሁን ደግሞ ሪፖብሊካን ተብሏል ። በመጨረሻ አየር መንገድ ውስጥ የሚሰራው ስራ ይመሰክራል ።